Sacred Texts  Bible  World Bible  Index  Previous  Next 

Amharic Bible: John

1:1 በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።

1:2 ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።

1:3 ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።

1:4 በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።

1:5 ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።

1:6 ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤

1:7 ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።

1:8 ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።

1:9 ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።

1:10 በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።

1:11 የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።

1:12 ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤

1:13 እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።

1:14 ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።

1:15 ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ።

1:16 እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤

1:17 ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።

1:18 መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።

1:19 አይሁድም። አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው።

1:20 መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ።

1:21 እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ።

1:22 እንኪያስ። ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት።

1:23 እርሱም። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ።

1:24 የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።

1:26 ዮሐንስ መልሶ። እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤

1:27 እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው።

1:28 ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።

1:29 በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።

1:30 አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።

1:31 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ።

1:32 ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።

1:33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።

1:34 እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።

1:35 በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥

1:36 ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።

1:37 ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።

1:38 ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ። ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም። ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው።

1:40 መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ።

1:41 ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ።

1:42 እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው።

1:43 ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው።

1:44 በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው።

1:45 ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ።

1:46 ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ። ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።

1:47 ናትናኤልም። ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ። መጥተህ እይ አለው።

1:48 ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ። ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።

1:49 ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ። ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው።

1:50 ናትናኤልም መልሶ። መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።

1:51 ኢየሱስም መልሶ። ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።

1:52 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።

2:1 በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤

2:2 ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።

2:3 የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው።

2:4 ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።

2:5 እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው።

2:6 አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር።

2:7 ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው።

2:8 አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም።

2:9 አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ።

2:10 ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።

2:11 ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።

2:12 ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ።

2:13 የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።

2:14 በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤

2:15 የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥

2:16 ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።

2:17 ደቀ መዛሙርቱም። የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ።

2:18 ስለዚህ አይሁድ መልሰው። ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት።

2:19 ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።

2:20 ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት።

2:21 እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።

2:22 ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።

2:23 በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ፤

2:24 ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።

3:1 ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ።

3:2 መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።

3:3 ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።

3:4 ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።

3:5 ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።

3:6 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።

3:7 ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።

3:8 ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።

3:9 ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው።

3:10 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?

3:11 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም።

3:12 ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?

3:13 ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።

3:14 ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።

3:16 በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።

3:17 ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።

3:18 በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።

3:19 ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።

3:20 ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤

3:21 እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።

3:22 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።

3:23 ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥

3:24 እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።

3:25 ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ።

3:26 ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት።

3:27 ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው እንዳች ሊቀበል አይችልም።

3:28 እናንተ። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን። ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ።

3:29 ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ።

3:30 እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።

3:31 ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው።

3:32 ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም።

3:33 ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ።

3:34 እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና።

3:35 አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል።

3:36 በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።

4:1 እንግዲህ። ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥

4:2 ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም።

4:4 በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት።

4:5 ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤

4:6 በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ።

4:7 ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም። ውኃ አጠጪኝ አላት፤

4:8 ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና።

4:9 ስለዚህ ሳምራዊቲቱ። አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና።

4:10 ኢየሱስ መልሶ። የእግዚአብሔርን ስጦታና። ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት።

4:11 ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?

4:12 በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው።

4:13 ኢየሱስም መልሶ። ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤

4:14 እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት።

4:15 ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው።

4:16 ኢየሱስም። ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ አላት።

4:17 ሴቲቱ መልሳ። ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስ። ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤

4:18 አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት።

4:19 ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ።

4:20 አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው።

4:21 ኢየሱስም እንዲህ አላት። አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል።

4:22 እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።

4:23 ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤

4:24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።

4:25 ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው።

4:26 ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት።

4:27 በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን። ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም። ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም።

4:28 ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም።

4:29 ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች።

4:30 ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

4:31 ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት።

4:32 እርሱ ግን። እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው።

4:33 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ። የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ።

4:34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።

4:35 እናንተ። ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ።

4:36 የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል።

4:37 አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና።

4:38 እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ።

4:39 ሴቲቱም። ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት።

4:40 የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ።

4:41 ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤

4:42 ሴቲቱንም። አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር።

4:43 ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ።

4:44 ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና።

4:45 ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለበዓል መጥተው ነበርና በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት።

4:46 ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ።

4:47 እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው።

4:48 ስለዚህም ኢየሱስ። ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው።

4:49 ሹሙም። ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው።

4:50 ኢየሱስም። ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ።

4:51 እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና። ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት።

4:52 እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም። ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት።

4:53 አባቱም ኢየሱስ። ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ።

4:54 ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው።

5:1 ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።

5:2 በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት።

5:3 በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።

5:4 አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር።

5:5 በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤

5:6 ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው።

5:7 ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።

5:8 ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው።

5:9 ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።

5:10 ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት።

5:11 እርሱ ግን። ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው።

5:12 እነርሱም። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት።

5:13 ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም።

5:14 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው።

5:15 ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ።

5:16 ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር።

5:17 ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።

5:18 እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።

5:19 ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።

5:20 አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።

5:21 አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።

5:22 ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።

5:24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።

5:25 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።

5:26 አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።

5:27 የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው።

5:28 በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።

5:30 እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።

5:31 እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤

5:32 ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ።

5:33 እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል።

5:34 እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ።

5:35 እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ።

5:36 እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና።

5:37 የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ መልኩንም አላያችሁም፤

5:38 እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም።

5:39 እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤

5:40 ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።

5:41 ከሰው ክብርን አልቀበልም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ እንደ ሌላችሁ አውቃችኋለሁ።

5:43 እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።

5:44 እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?

5:45 እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው።

5:46 ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።

5:47 መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?

6:1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው።

6:2 በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።

6:3 ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።

6:4 የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር።

6:5 ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን። እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው።

6:6 ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ።

6:7 ፊልጶስ። እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት።

6:8 ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ።

6:9 አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል? አለው።

6:10 ኢየሱስም። ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር።

6:11 ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን።

6:12 ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን። አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ አላቸው።

6:13 ሰለዚህ አከማቹ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ።

6:14 ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ። ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ።

6:15 በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ።

6:16 በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፥

6:17 በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። አሁንም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤

6:18 ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ።

6:19 ሀያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ።

6:20 እርሱ ግን። እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው።

6:21 ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች።

6:22 በነገው በባሕር ማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ፤

6:23 ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ።

6:24 ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ፥ ራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ።

6:25 በባሕር ማዶም ሲያገኙት። መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ? አሉት።

6:26 ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም።

6:27 ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።

6:28 እንግዲህ። የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት።

6:29 ኢየሱስ መልሶ። ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው።

6:30 እንግዲህ። እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ?

6:31 ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት።

6:32 ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤

6:33 የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው።

6:34 ስለዚህ። ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት።

6:35 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።

6:36 ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ።

6:37 አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤

6:38 ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።

6:39 ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው።

6:40 ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።

6:41 እንግዲህ አይሁድ። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና።

6:42 አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ።

6:43 ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ።

6:44 የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።

6:45 ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።

6:46 አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል።

6:47 እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።

6:48 የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።

6:49 አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤

6:50 ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።

6:51 ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።

6:52 እንግዲህ አይሁድ። ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።

6:53 ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።

6:54 ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።

6:55 ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።

6:56 ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።

6:57 ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።

6:58 ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል

6:59 በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ።

6:60 ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ። ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ።

6:61 ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው። ይህ ያሰናክላችኋልን?

6:62 እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?

6:63 ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።

6:64 ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።

6:65 ደግሞ። ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ።

6:66 ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።

6:67 ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ። እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ።

6:68 ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤

6:69 እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት።

6:70 ኢየሱስም። እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው።

6:71 ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና።

7:1 ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር።

7:2 የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር።

7:3 እንግዲህ ወንድሞቹ። ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤

7:4 ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት።

7:5 ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና።

7:6 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው።

7:7 ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል።

7:8 እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም።

7:9 ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ።

7:10 ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ።

7:11 አይሁድም። እርሱ ወዴት ነው? እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር።

7:12 በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም። ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን። አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር።

7:13 ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር።

7:14 አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር።

7:15 አይሁድም። ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር።

7:16 ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤

7:17 ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል።

7:18 ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም።

7:19 ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?

7:20 ሕዝቡ መለሱና። ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል? አሉት።

7:21 ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ።

7:22 ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ።

7:23 የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን?

7:24 ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።

7:25 እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ። ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን?

7:26 እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን?

7:27 ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።

7:28 እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር። እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤

7:29 እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ ብሎ ጮኸ።

7:30 ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም።

7:31 ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና። ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን? አሉ።

7:32 ፈሪሳውያንም ሕዝቡ ሰለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጕሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ።

7:33 ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ።

7:34 ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ።

7:35 እንግዲህ አይሁድ። እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን?

7:36 እርሱ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው? ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።

7:37 ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ። ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ።

7:38 በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ።

7:39 ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።

7:40 ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ። ይህ በእውነት ነቢዩ ነው አሉ፤

7:41 ሌሎች። ይህ ክርስቶስ ነው አሉ፤ ሌሎች ግን። ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን?

7:42 ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን? አሉ።

7:43 እንግዲህ ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤

7:44 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ወደዱ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም።

7:45 ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነዚያም። ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው? አሉአቸው።

7:46 ሎሌዎቹ። እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ።

7:47 እንግዲህ ፈሪሳውያን። እናንተ ደግሞ ሳታችሁን?

7:48 ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን?

7:49 ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው።

7:50 ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ።

7:51 ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።

7:52 እነርሱም መለሱና። አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት።

7:53 እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።

8:1 ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።

8:2 ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር።

8:3 ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው።

8:4 መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች።

8:5 ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።

8:6 የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤

8:7 መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።

8:8 ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ።

8:9 እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች።

8:10 ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ። አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት።

8:11 እርስዋም። ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም። እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።

8:12 ደግሞም ኢየሱስ። እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።

8:13 ፈሪሳውያንም። አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም አሉት።

8:14 ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም።

8:15 እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም።

8:16 የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው።

8:17 የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል።

8:18 ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።

8:19 እንግዲህ። አባትህ ወዴት ነው? አሉት። ኢየሱስ መልሶ። እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር አላቸው።

8:20 ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም።

8:21 ኢየሱስም ደግሞ። እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው።

8:22 አይሁድም። እኔ ወደ ምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ አሉ።

8:23 እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።

8:24 እንግዲህ። በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው።

8:25 እንግዲህ። አንተ ማን ነህ? አሉት። ኢየሱስም። ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ።

8:26 ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ አላቸው።

8:27 ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።

8:28 ስለዚህም ኢየሱስ። የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ።

8:29 የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም አላቸው።

8:30 ይህን ሲናገር ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

8:31 ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ። እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤

8:32 እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው።

8:33 እነርሱም መልሰው። የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ። አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት።

8:34 ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው።

8:35 ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል።

8:36 እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ።

8:37 የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ።

8:38 እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ።

8:39 መልሰውም። አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም። የአብሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር።

8:40 ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም።

8:41 እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት።

8:42 ኢየሱስም አላቸው። እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና።

8:43 ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው።

8:44 እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።

8:45 እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም።

8:46 ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም?

8:47 ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም።

8:48 አይሁድ መልሰው። ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን? አሉት።

8:49 ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እኔስ ጋኔን የለብኝም ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ።

8:50 እኔ ግን የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ።

8:51 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም።

8:52 አይሁድ። ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን። አብርሃም ስንኳ ሞተ ነቢያትም፤ አንተም። ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አይቀምስም ትላለህ።

8:53 በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማንን ታደርጋለህ? አሉት።

8:54 ኢየሱስም መለሰ አለም። እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤

8:55 አላወቃችሁትምም፥ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ ቃሉንም እጠብቃለሁ።

8:56 አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው።

8:57 አይሁድም። ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት።

8:58 ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።

8:59 ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ።

9:1 ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ።

9:2 ደቀ መዛሙርቱም። መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት።

9:3 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም።

9:4 ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች።

9:5 በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ።

9:6 ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና።

9:7 ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ።

9:8 ጐረቤቶቹም ቀድሞም ሲለምን አይተውት የነበሩ። ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረ አይደለምን? አሉ።

9:9 ሌሎች። እርሱ ነው አሉ፤ ሌሎች። አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ አሉ፤ እርሱ። እኔ ነኝ አለ።

9:10 ታድያ። ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ? አሉት።

9:11 እርሱ መልሶ። ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ አይኖቼን ቀባና። ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ አለ።

9:12 ያ ሰው ወዴት ነው? አሉት። አላውቅም አለ።

9:13 በፊት ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት።

9:14 ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ።

9:15 ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም። ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም አላቸው።

9:16 ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ። ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ። ሌሎች ግን። ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል? አሉ።

9:17 በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። ከዚህም የተነሣ ዕውሩን። አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ደግሞ አሉት። እርሱም። ነቢይ ነው አለ።

9:18 አይሁድ የዚያን ያየውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም ስለ እርሱ አላመኑም፥

9:19 እነርሱንም። እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል? ብለው ጠየቁአቸው።

9:20 ወላጆቹም መልሰው። ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ አናውቃለን፤

9:21 ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል አሉ።

9:22 ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፤ እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና።

9:23 ስለዚህ ወላጆቹ። ሙሉ ሰው ነው፥ ጠይቁት አሉ።

9:24 ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው ሁለተኛ ጠርተው። እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን አሉት።

9:25 እርሱም መልሶ። ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ አለ።

9:26 ደግመውም። ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ? አሉት።

9:27 እርሱም መልሶ። አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን? አላቸው።

9:28 ተሳድበውም። አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤

9:29 እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት።

9:30 ሰውዬው መለሰ እንዲህም አላቸው። ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ።

9:31 እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን።

9:32 ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤

9:33 ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር።

9:34 መልሰው። አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን? አሉት። ወደ ውጭም አወጡት።

9:35 ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም። አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው።

9:36 እርሱም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ።

9:37 ኢየሱስም። አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው።

9:38 እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም።

9:39 ኢየሱስም። የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ አለ።

9:40 ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው። እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን? አሉት።

9:41 ኢየሱስም አላቸው። ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን። እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።

10:1 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤

10:2 በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው።

10:3 ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።

10:4 የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤

10:5 ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።

10:6 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም።

10:7 ኢየሱስም ደግሞ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ።

10:8 ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም።

10:9 በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል።

10:10 ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።

10:11 መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።

10:12 እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።

10:13 ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።

10:14 መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።

10:16 ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።

10:17 ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል።

10:18 እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።

10:19 እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ።

10:20 ከእነርሱም ብዙዎች። ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ።

10:21 ሌሎችም። ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን? አሉ።

10:22 በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤

10:23 ክረምትም ነበረ። ኢየሱስም በመቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር።

10:24 አይሁድም እርሱን ከበው። እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት።

10:25 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤

10:26 እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።

10:27 በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤

10:28 እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።

10:29 የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።

10:30 እኔና አብ አንድ ነን።

10:31 አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ።

10:32 ኢየሱስ። ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው።

10:33 አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት።

10:34 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?

10:35 መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥

10:36 የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?

10:37 እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤

10:38 ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።

10:39 እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ።

10:40 ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ።

10:41 ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው። ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ።

10:42 በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

11:1 ከማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢታንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር።

11:2 ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር።

11:3 ስለዚህ እኅቶቹ ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል ብለው ወደ እርሱ ላኩ።

11:4 ኢየሱስም ሰምቶ። ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ።

11:5 ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር።

11:6 እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤

11:7 ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ። ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው።

11:8 ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን? አሉት።

11:9 ኢየሱስም መልሶ። ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤

11:10 በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው።

11:11 ይህን ተናገረ፤ ከዚህም በኋላ። ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው።

11:12 እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ። ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት።

11:13 ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው።

11:14 እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ። አልዓዛር ሞተ፤

11:15 እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው።

11:16 ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት። ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ።

11:17 ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው።

11:18 ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች።

11:19 ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር።

11:20 ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር።

11:21 ማርታም ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤

11:22 አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው።

11:23 ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት።

11:24 ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።

11:25 ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤

11:26 ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።

11:27 እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው።

11:28 ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ። መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል አለቻት።

11:29 እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤

11:30 ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር።

11:31 ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት።

11:32 ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው።

11:33 ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤

11:34 ወዴት አኖራችሁት? አለም። እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት።

11:35 ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።

11:36 ስለዚህ አይሁድ። እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ አሉ።

11:37 ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ። ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን? አሉ።

11:38 ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር።

11:39 ኢየሱስ። ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ። ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው።

11:40 ኢየሱስ። ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት።

11:41 ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ። አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ።

11:42 ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ።

11:43 ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ። አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።

11:44 የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም። ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው።

11:45 ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤

11:46 ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው።

11:47 እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው። ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና።

11:48 እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ።

11:49 በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤

11:50 ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው።

11:51 ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤

11:52 ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ።

11:53 እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።

11:54 ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።

11:55 የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካ በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።

11:56 ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በመቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው። ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን? ተባባሉ።

11:57 የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ እርሱ ያለበትን ስፍራ የሚያውቀው ሰው ቢኖር እንዲያመለክታቸው አዘው ነበር።

12:1 ከፋሲካም በፊት በስድስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ።

12:2 በዚያም እራት አደረጉለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት አንዱ ነበረ።

12:3 ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ።

12:4 ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ።

12:5 ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ።

12:6 ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው።

12:7 ኢየሱስም። ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤

12:8 ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ።

12:9 ከአይሁድም ብዙ ሕዝብ በዚያ እንደ ነበረ አውቀው መጡ፥ ከሙታንም ያስነሣውን አልዓዛርን ደግሞ እንዲያዩ ነበረ እንጂ ስለ ኢየሱስ ብቻ አይደለም።

12:10 የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፥

12:11 ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና።

12:12 በማግሥቱ ወደ በዓሉ መጥተው የነበሩ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ፥

12:13 የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ።

12:14 አንቺ የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ።

12:16 ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው።

12:17 አልዓዛርንም ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ሲያስነሣው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ይመሰክሩለት ነበር።

12:18 ስለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ይህን ምልክት እንዳደረገ ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ።

12:19 ሰለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው። አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ።

12:20 በበዓሉም ሊሰግዱ ከወጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤

12:21 እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው። ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት።

12:22 ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት።

12:23 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል።

12:24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።

12:25 ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።

12:26 የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።

12:27 አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ።

12:28 አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም። አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።

12:29 በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ። ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች። መልአክ ተናገረው አሉ።

12:30 ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም።

12:31 አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤

12:32 እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።

12:33 በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ።

12:34 እንግዲህ ሕዝቡ። እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው? ብለው መለሱለት።

12:35 ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም።

12:36 የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው።

12:37 ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም።

12:39 ኢሳይያስ ደግሞ። በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም አደነደነ ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው።

12:41 ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ።

12:42 ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤

12:43 ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።

12:44 ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ። በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤

12:45 እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል።

12:46 በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።

12:47 ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም።

12:48 የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።

12:49 እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ።

12:50 ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።

13:1 ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።

13:2 እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥

13:3 ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥

13:4 ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤

13:5 በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ።

13:6 ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው።

13:7 ኢየሱስም መልሶ። እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው።

13:8 ጴጥሮስም። የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም አለው። ኢየሱስም። ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት።

13:9 ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው።

13:10 ኢየሱስም። የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው።

13:11 አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ። ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም አለው።

13:12 እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው። ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?

13:13 እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ።

13:14 እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል።

13:15 እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።

13:16 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም።

13:17 ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።

13:18 ስለ ሁላችሁ አልናገርም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ። እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው።

13:19 በሆነ ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፥ ከአሁን ጀምሬ አስቀድሞ ሳይሆን እነግራችኋለሁ።

13:20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

13:21 ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ታወከ መስክሮም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል አለ።

13:22 ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ አመንትተው እርስ በርሳቸው ተያዩ።

13:23 ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤

13:24 ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ። ስለማን እንደ ተናገረ ንገረን አለው።

13:25 እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነው? አለው።

13:26 ኢየሱስም። እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው።

13:27 ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ። የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው።

13:28 ነገር ግን ከተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው ማንም አላወቀም፤

13:29 ይሁዳ ከረጢቱን የያዘ ስለ ሆነ፥ ኢየሱስ። ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፥ ወይም ለድሆች ምጽዋት እንዲሰጥ ያለው ለአንዳንዱ መስሎአቸው ነበርና።

13:30 እርሱም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ።

13:31 ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ። አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ፤

13:32 እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል።

13:33 ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም። እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ።

13:34 እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።

13:35 እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።

13:36 ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ? አለው። ኢየሱስም። ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ ብሎ መለሰለት።

13:37 ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ አለው።

13:38 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት። ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።

14:1 ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።

14:2 በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤

14:3 ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።

14:4 ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ።

14:5 ቶማስም። ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው።

14:6 ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።

14:7 እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።

14:8 ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።

14:9 ኢየሱስም አለው። አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ?

14:10 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።

14:11 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።

14:12 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥

14:13 እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።

14:14 ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።

14:15 ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤

14:17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።

14:18 ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።

14:19 ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ።

14:20 እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።

14:21 ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።

14:22 የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ። ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው? አለው።

14:23 ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።

14:24 የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።

14:25 ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤

14:26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።

14:27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።

14:28 እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር።

14:29 ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን። ነግሬአችኋለሁ።

14:30 ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤

14:31 ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።

15:1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው።

15:2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።

15:3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤

15:4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።

15:5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።

15:6 በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል።

15:7 በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።

15:8 ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።

15:9 አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ።

15:10 እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።

15:11 ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ።

15:12 እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።

15:13 ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።

15:14 እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።

15:15 ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።

15:16 እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።

15:17 እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ።

15:18 ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ።

15:19 ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።

15:20 ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ።

15:21 ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ሰለ ስሜ ያደርጉባችኋል።

15:22 እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም።

15:23 እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል።

15:24 ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደረግሁ፥ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል።

15:25 ነገር ግን በሕጋቸው። በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

15:26 ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤

15:27 እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።

16:1 እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ።

16:2 ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል።

16:3 ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው።

16:4 ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእንናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም።

16:5 አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም። ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም።

16:6 ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል።

16:7 እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።

16:8 እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤

16:9 ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤

16:11 ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።

16:12 የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም።

16:13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።

16:14 እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።

16:15 ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ። ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።

16:16 ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።

16:17 ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፤ ደግሞ። ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ።

16:18 እንግዲህ። ጥቂት የሚለው ይህ ምንድር ነው? የሚናገረውን አናውቅም አሉ።

16:19 ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁ ስላልሁ፥ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን?

16:20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ ታለቅሳለችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፥ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፥ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።

16:21 ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና ስለ ደስታዋ መከራዋን ኋላ አታስበውም።

16:22 እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።

16:23 በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።

16:24 እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ።

16:25 ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ ለእናንተ በግልጥ የምናገርበት እንጂ ከዚያ ወዲያ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል።

16:26 በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤

16:27 እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና።

16:28 ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።

16:29 ደቀ መዛሙርቱ። እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ በምሳሌም ምንም አትነግርም።

16:30 ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት።

16:31 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። አሁን ታምናላችሁን?

16:32 እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፥ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም።

16:33 በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።

17:1 ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።

17:3 እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።

17:4 እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤

17:5 አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።

17:6 ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤

17:7 ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤

17:8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ።

17:9 እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤

17:10 የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው የአንተውም የእኔ ነው፤ እኔም ስለ እነርሱ ከብሬአለሁ።

17:11 ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።

17:12 ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም።

17:13 አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ።

17:14 እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው።

17:15 ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም።

17:16 እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።

17:17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።

17:18 ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤

17:19 እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።

17:20 ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።

17:22 እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።

17:24 አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።

17:25 ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤

17:26 እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።

18:1 ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ።

18:2 ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር።

18:3 ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ከካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ።

18:4 ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና። ማንን ትፈልጋላችሁ አላቸው።

18:5 የናዝሬቱን ኢየሱስን ብለው መለሱለት። ኢየሱስ። እኔ ነኝ አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር።

18:6 እንግዲህ። እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ።

18:7 ደግሞም። ማንን ትፈልጋላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። የናዝሬቱን ኢየሱስን አሉት።

18:8 ኢየሱስ መልሶ። እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው አለ፤

18:9 ይህም። ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

18:10 ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ።

18:11 ኢየሱስም ጴጥሮስን። ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን? አለው።

18:12 እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፥

18:13 አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና።

18:14 ቀያፋም። አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ ይሻላል ብሎ ለአይሁድ የመከራቸው ነበረ።

18:15 ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤

18:16 ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው።

18:17 በረኛ የነበረችይቱም ገረድ ጴጥሮስን። አንተ ደግሞ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን? አለችው። እርሱ። አይደለሁም አለ።

18:18 ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር።

18:19 ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።

18:20 ኢየስስም መልሶ። እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም።

18:21 ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ አለው።

18:22 ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ። ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን? ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው።

18:23 ኢየሱስም መልሶ። ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ሰለ ምን ትመታኛለህ? አለው።

18:24 ስለዚህ ሐና እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሰደደው።

18:25 ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። እንግዲህ። አንተ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ አይደለህምን? አሉት። እርሱም። አይደለሁም ብሎ ካደ።

18:26 ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ። በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበረምን? አለው።

18:27 ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

18:28 ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም የፋሲካ በግ ይበሉ ዘንድ እንጂ እንዳይረክሱ ወደ ገዡ ግቢ አልገቡም።

18:29 ስለዚህ ጲላጦስ ወደ ውጭ ወደ እነርሱ ወጥቶ። ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ አላቸው።

18:30 እነርሱም መልሰው። ይህስ ክፉ አድራጊ ባይሆን ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር አሉት።

18:31 ጲላጦስም። እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት አላቸው። አይሁድም። ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም አሉት፤

18:32 ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት ሊሞት እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

18:33 ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው።

18:34 ኢየሱስም መልሶ። አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው።

18:35 ጲላጦስ መልሶ። እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል? አለው።

18:36 ኢየሱስም መልሶ። መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው።

18:37 ጲላጦስም። እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው።

18:38 ጲላጦስ። እውነት ምንድር ነው? አለው። ይህንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም።

18:39 ነገር ግን በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን? አላቸው።

18:40 ሁሉም ደግመው። በርባንን እንጂ ይህን አይደለም እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።

19:1 በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው።

19:2 ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤

19:3 እየቀረቡም። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ይሉት ነበር፤

19:4 በጥፊም ይመቱት ነበር። ጲላጦስም ደግሞ ወደ ውጭ ወጥቶ። እነሆ፥ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ አላቸው።

19:5 ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀይ ልብስም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ።

19:6 ጲላጦስም። እነሆ ሰውዬው አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎች ባዩትም ጊዜ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት አላቸው።

19:7 አይሁድም መልሰው። እኛ ሕግ አለን፥ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፥ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና አሉት።

19:8 ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤

19:9 ተመልሶም ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን። አንተ ከወዴት ነህ? አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም።

19:10 ስለዚህ ጲላጦስ። አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን? አለው።

19:11 ኢየሱስም መልሶ። ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው አለው።

19:12 ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ። ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ።

19:13 ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፥ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው ጸፍጸፍ በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ።

19:14 ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓትም የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም። እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው።

19:15 እነርሱ ግን። አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። ንጉሣችሁን ልስቀለውን? አላቸው። የካህናት አለቆችም። ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም ብለው መለሱለት።

19:16 ስለዚህ በዚያን ጊዜ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው።

19:17 ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ።

19:18 በዚያም ሰቀሉት፥ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በዚህ አንዱን በዚያ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ።

19:19 ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም። የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚል ነበረ።

19:20 ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር።

19:21 ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን። እርሱ። የአይሁድ ንጉስ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ አሉት።

19:22 ጲላጦስም። የጻፍሁትን ጽፌአለሁ ብሎ መለሰ።

19:23 ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም።

19:24 ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

19:25 ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።

19:26 ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት።

19:27 ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።

19:28 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ።

19:29 በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት።

19:30 ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።

19:31 አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት።

19:32 ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤

19:33 ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤

19:34 ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ።

19:35 ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል።

19:36 ይህ የሆነ። ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው።

19:37 ደግሞም ሌላው መጽሐፍ። የወጉትን ያዩታል ይላል።

19:38 ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ።

19:39 ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ።

19:40 የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት።

19:41 በተሰቀለበትም ስፍራ አትክልት ነበረ፥ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ።

19:42 ስለዚህ መቃብሩ ቅርብ ነበረና ስለ አይሁድ ማዘጋጀት ቀን ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።

20:1 ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።

20:2 እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ። ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው።

20:3 ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ።

20:4 ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤

20:5 ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም።

20:6 ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥

20:7 ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ።

20:8 በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤

20:9 ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና።

20:10 ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ።

20:11 ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤

20:12 ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።

20:13 እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም። ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው።

20:14 ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።

20:15 ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው።

20:16 ኢየሱስም። ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው።

20:17 ኢየሱስም። ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።

20:18 መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።

20:19 ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።

20:20 ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።

20:21 ኢየሱስም ዳግመኛ። ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው።

20:22 ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።

20:23 ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።

20:24 ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም።

20:25 ሌሎቹም ደቀ መዛሙርቱ። ጌታን አይተነዋል አሉት። እርሱ ግን። የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው።

20:26 ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።

20:27 ከዚያም በኋላ ቶማስን። ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።

20:28 ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።

20:29 ኢየሱስም። ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።

20:30 ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤

20:31 ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።

21:1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና ተገለጠላቸው፤

21:2 እንዲህም ተገለጠ። ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ከገሊላ ቃና የሆነ ናትናኤልም የዘብዴዎስም ልጆች ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ።

21:3 ስምዖን ጴጥሮስ። ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ አላቸው። እነርሱም። እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ በዚያችም ሌሊት ምንም እላጠመዱም።

21:4 በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም።

21:5 ኢየሱስም። ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። የለንም ብለው መለሱለት።

21:6 እርሱም። መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው።

21:7 ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን። ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ።

21:8 ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።

21:9 ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ።

21:10 ኢየሱስም። አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ አላቸው።

21:11 ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንም ያህል ብዙ ሲሆን መረቡ አልተቀደደም።

21:12 ኢየሱስም። ኑ፥ ምሳ ብሉ አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ ስንኳ። አንተ ማን ነህ? ብሎ ሊመረምረው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና።

21:13 ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፥ እንዲሁም ዓሣውን።

21:14 ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ።

21:15 ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው።

21:16 ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው።

21:17 ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ።

21:18 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው።

21:19 በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ። ተከተለኝ አለው።

21:20 ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው? ያለው ነበረ።

21:21 ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል? አለው።

21:22 ኢየሱስም። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ አለው።

21:23 ስለዚህ። ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አለው እንጂ አይሞትም አላለውም።

21:24 ስለ እነዚህም የመሰከረ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፥ ምስክሩም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።

21:25 ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።


Next: Acts